የእንሰሳት ልማት ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ተግባርና ኃላፊነት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራውን በስፋት ማስቀጠል ነው፡፡ የእንስሳት ልማት አጀንዳ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ዝርያ ማሻሻል በዋነኝነት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የእንስሳቱ ከምርታማነት፣ ሥነ-ተዋልዶ ባህሪ፣ የጤናና የዕድገት ባህሪያት ብቃት መረጃ በዘር-ሐረጋቸው መሰረት በአግባቡ ተሰብስቦ፣ ተደራጅቶ፣ ተይዞና ተተንትኖ በማሰራጨት ጥቅም ላይ ሲውል ነው።የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ በዋናነት ከምርታማነት፣ ሥነ-ተዋልዶ ባህሪ፣ የጤናና የዕድገት መረጃዎች ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያለው በመሆኑ የወተት ከብት ዝርያን ለማሻሻል እየተሰሩ ካሉ ተግባራት መካከል የወተት ከብት መረጃ ምዝገባ ማዕከልን በብሄራዊ ደረጃ ማጠናከርና የአርቢዎችን ግብረ መልስ ስርዓት ማጠናከር ነው፡፡ የወተት ከብት ዝርያ መረጃ ምዝገባ ስራ ለዝርያ ማሻሻያና አርቢው የሚያረባቸውን እንስሳት መረጃ ላይ ተንተርሶ እርባታውን አዘምኖ ለማካሄድና አርቢዎች ገቢያቸው መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማገዙም በላይ ለፖሊሲ የሚሆን መረጃ ማመንጨት የሚያስችል ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የወተት ከብት ዝርያ ማሻሻያ ላይ ያለውን የምርታማነት፣ ሥነ-ተዋልዶ ባህሪ፣ የጤናና የዕድገት መረጃዎች ምዝገባን በዘላቂነት ማከናወን አስፈላጊ ነው፡፡